የኡስታዝ አቡበከር አህመድ የምስጋና እና የደስታ መግለጫ!

አልሃምዱሊላህ፣ አልሃምዱሊላህ፣ አልሃምዱሊላህ!

ያለልዩነት ሲነሳ የኖረ የተቋም ጥያቄ ያለልዩነት ወደመፍትሄ በማምራቱ እንኳን ደስ አለን፣ እንኳን ደስ አላችሁ!

ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ያለአንዳች ልዩነት ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ በጋራ ሲያነሱት የቆዩትና መሰዋእትነት የከፈሉለት የነፃና እና ገለልተኛ ተቋም ጥያቄ ዛሬ በተካሄደው የተቋማዊ ለውጥ እና የአንድነት ጉባኤ አንድ ወሳኝ እርከን ተሸግሯል፡፡

ለሰባት አመታት እልህ አስጨራሽ ትግል የተደረገበትና ብዙዎች ህይወታቸውን አጥተው፣ ሺዎች ታስረውና ተሰደው ዋጋ የከፈሉለት የዘመናት የህዝብ ጥያቄ ዛሬ የመፍትሄ ብርሃን ማየት ችሏል፡፡

ለአስራ አንድ ወራት በክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ አነሳሽነት በተቋቋመው የተቋማዊ ለውጥ የጋራ ኮሚቴ እልህ አስጨራሽ ጥረት ሲደከምበት የነበሩ ስራዎች ዛሬ በኡለማወች ሙሉ ድጋፍ እና በልዩ የወንድማማችነት ስሜት ከዳር ደርሷል፡፡
በድጋሜ ምስጋና ለአለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን!

የተከበራችሁ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች
የሀገሪቱ ግማሽ አካል ሆነን ሳለ በደካማ ተቋምና በብልሹ አሰራር የተተበተቡ አመራሮች ተወክለን በሀገራችን ማግኘት የሚገባንን ጥቅምም ሆነ ለሀገራችን ልናበረክተው የሚገባንን አስተዋፅ አንቆ የያዘን አንዱ የመጅሊስ ጉዳይ ነበር፡፡ የመጅሊስ ጉዳይ ከተቋም ጥያቄ በላይ የስነልቦና ጉዳይም ሆኖ ሙስሊሙ ሀገራዊ ሚናውን ከመወጣት ይልቅ በዚሁ ብቻ በመጠመድ ለልዩነት እና አቅምን ያለቦታው እንዲያባክኑ ተገደዋል፡፡ ይህ ዘመን ዛሬ ሊያበቃ ይገባል፡፡ ሁሉም በመሰለው መንገድ ለጠንካራ ተቋም ታግሏል፡፡ አላህ ደግሞ በፈለገው መልኩ ዛሬን አሳይቶናል፡፡ መጪው ግዜ ብዙ ስራ የሚሰራበት ቢሆንም የተገኘው ውጤት ግን እንደ ትልቅ ስኬት የሚቆጠር ነውና በስኬቱ ደስም ይበላችሁ አላህንም የተግባር አመስጋኝ ሁኑ፡፡ የቀድሞው የመጅሊስ አመራሮችም ለለውጡ ያሳያችሁት ቀና መተባበር ለናንተም ለህዝቡም ትክክለኛው ውሳኔ ነውና በውሳኔያችሁ ኩሩ፡፡

የተከበራችሁ የሀገራችን ህዝቦች

ባሳለፍናቸው ሰባት አመታት ባደረግነው የመብት ማስከበር ትግል የተከፈተብ ፕሮፓጋንዳ ሳይበግራችሁ ጥያቄአችን ሙሉ ለሙሉ የኢትዮጵያ ፖለቲካ የፈጠረው ሀገራዊ ችግር መሆኑን በመረዳት በሁሉም መልኩ ከጎናችሁ ቆማችኋልና ዛሬ የተደረሰበት ስኬት የናንተም ነውና እንኳን ደስ አላችሁ፡፡ በቀጣይም በሚኖረን የቡድን እና የጋራ የመብት ጥያቄና ሀገራዊ ሚና አብሮነታችን እንደሚቀጥልም እምነቴ ነው፡፡

ለክቡር ዶክተር አብይ አህመድ መንግስት

ክቡር ዶክተር አብይ አህመድ በሀገራችን ታሪክ ቀናነትን እና የይቻላል መንፈስን ከልብ የሚያምኑ መሪ ናቸው፡፡ የሚያምኑበትንም ወደተግባር ለመቀየር ቁርጠኛ የሆኑ መሪ ናቸው፡፡ ይህንን ቁርጠኝነታቸውን በተለያዩ ሀገራዊ አጋጣሚዎች ያየን ቢሆንም በህዝበ ሙስሙ የመብት ጥያቄና የጠንካራ ተቋም አስፈልጎት ላይ ግን ከኛ ያላነሰ ግልፅ አቋምና ጠንካራ አቋም ነበራቸው፡፡ ይህንን ምኖታቸው እውን እንዲሆን ባደረጉልን ያልተቋረጠ ድጋፍ ዛሬ ላይ ደርሷልና እንኳን ደስ አለዎት ለማለት እፈልጋለሁ፡፡

ክብርት ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል የሰላም ሚኒስትር እንደመሆናቸው፣ የሙስሊሙ ማህበረሰብ አባል እንደመሆናቸው፣ ቅን አመራርን መርሁ ያደረገው የዶክተር አብይ መንግስት አካል እንደመሆናቸው ለዚህ ስራ ከፊት ተሰልፈው ሲያግዙን ነበርና ምስጋናዬን አቀርባለሁ፣ እንኳን ደስ አለዎት ለማለትም እፈልጋለሁ፡፡

ምክትል ጠቅላይሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በተለይም በመጨረሻዎቹ ወቅቶች ለነበራቸው ቁርጠኛ ድጋፍ ላመሰግን እወዳለሁ።

ክቡር አቶ ለማ መገርሳ የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትን የተለጠፈባቸውን ስም ውድቅ በማድረግ በሀገርና በህዝብ ጉዳይ ከጎናቸው አድርገው በማሰለፍ የመጀመሪያውን ሚና የተጫወቱ ነበሩና ላመሰግናቸው እወዳለሁ።

ክቡር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በተለይም በክልል ደረጃ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት ላሳዩን ቀናነት ላመሰግን እወዳለሁ። እንዲሁም ለአጠቃላይ በመንግስት ውስጥ ላለው የለውጥ ሀይል ከፍተኛ ምስጋናዬን ለማቅረብ እፈልጋለሁ።

የተከበራችሁ ኡለማዎች እና ምሁራን፣

ትላንት በኡለሞቻችን ሙሉ ስምምነት የፀደቁት የህግ፣ የመዋቅር እና የኡለሞች መግባቢያ ሰነዶች በጉባኤው ተሳታፊዎች ቅን ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ነውና ትግበራውም የሁሉንም ቁርጠኛ ድጋፍ ይፈልጋል፡፡ በተለይም አዲስ የተቋቋመው ግዚያዊ የኡለሞች ምክር ቤት እና ቦርድ ስራውን ዛሬ ነገ ሳይል እንዲጀምር እያስታወስኩ ለስራው መሳካት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደምናደርግ ለመግለፅ እወዳለሁ፡፡ በመጨረሻም ከፊታችን ያለው ረመዳን ዛሬ በፈጠርነው የአንድነት፣ የሰላም፣ የእርቅ እና የለውጥ መንፈስ እንድንይዘው ላደረገን አላህ ምስጋናዬን እያቀረብኩ ከወዲሁ የተባረከ የረመዳን ወር እንዲሆንልን እመኛለሁ፡፡

Leave a comment