ስለ እኔ

ስለ ኡስታዝ አቡበክር አህመድ

ኡስታዝ አቡበከር አህመድ ከአባቱ ሀጅ አህመድ ሙሃመድ እና ከእናቱ ኸድጃ ኢብራሂም በደሴ ከተማ ፒያሳ አካባቢ ተወለደ፡፡ኡስታዝ አቡበከር ለቤተሰቦቹ አምስተኛ ልጅ ሲሆን እጅግ ተዎዳጅና በስነ-ምግባሩም የላቀ ነበር፡፡ አካዳሚካል ት/ቱን በጦሳ ት/ቤት የተማረ ሲሆን እስከ 12ኛ ደረጃ ተምሯል፡፡ አቡበከርን ጓደኞቹና የቅርብ ሰዎች “በክሪ” እያሉ ነበር የሚጠሩት፡፡በክሪ በልጅነት እድሜው ከኢስላም አደብ ወጣ ብሎ የነበረ ሲሆን አባቱ ሀጅ አህመድ ያቀሩት የነበረው ኢስላማዊ ት/ት መልሶ ወደ ዲኑ ጠልቆ እንዲገባ ረድቶታል፡፡ በልጅነቱ ኪታብ ይቀራ የነበረው አባቱ ሀጅ አህመድ ጋር ቢሆንም በታላቁ ዓሊም ሀጅ ሸኽ አደም (የአረብ ገንዳ መስጅድ ኢማም) ጋር ብዙ ኪታቦችን ቀርቷል፡፡ ከልጅነቱ ጀምሮ ከጓደኞቹ ለየት የሚያደርገው ታላቅ የማስታዎስ ችሎታውና ለጓደኞቹ የነበረው ቅን የሆነ አስተሳሰብ ነው፡፡ ለእውቀት የነበረው ጉጉትና ፍቅርም ይህ ነው አይባልም፡፡ በክሪ እጅግ አዛኝና ሩህሩህም ነበር፡፡ የረሱልን (ሰ.ዐ.ወ) ሱናዎች በመከተል ከጓደኞቹ ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል፤ በተለይ ግን ሽቱ በጣም ይዎድ ነበር፡፡ለዲኑ ተቁርቋሪና አርቆ አሳቢም ነበር፡፡ አሏህ ከምንም በላይ የማስታዎስ ችሎታን ሰጥቶታል፡፡ ብዙዎችን የሚያስገርመው ደግሞ የንግግር ፍጥነቱ ካሰበው ንግግር ጋር አለመጋጨቱና ከያዘው ርዕስ አለማስወጣቱ ነው፡፡ በክሪ ለዲኑ ሲል ብዙ ያደረገና እያደረገ ያለ፤ለብዙ ወጣቶች አርኣያም መሆን የቻለ ታላቅ ሰው ነው፡፡ ኢስላምን ለማገልገል የቻለውን ያህል የሚተጋ፤ በተላያዩ መስጅዶች እየተንቀሳቀሰ የተለያዩ ትምህርቶችን የሰጠ ቢሆንም በኋላ ላይ ግን ሲዲዎችን በማሳተም ሰዎችን በእውቀት ለመገንባት ችሏል፡፡ በክሪ ከልጅነቱ ጀምሮ ተሰሚነት የነበረው ሲሆን የሚገርመው ደግሞ ማንም በምንም መልኩ ሊሸውደው አለመቻሉ ነው፡፡ ትንሽ ቁጠኛ ቢሆንም እጅግ ቸርና ለጋስ እንደነበር ማንም ያውቀዋል፡፡ በክሪ ለዚህ ኡማ ታላቅ ነገር ለማበርከት የቻለ ታላቅ ሰው ነው፡፡ ለቆመለት አላማ ወደኋላን የማያውቅ ለኃይማኖቱ ተቆርቋሪና ታጋይ፤ ለኢስላም ሲል ህይወቱን አሳልፎ ለመስጠት ዝግጁ የሆነ ድንቅ ሰው፡፡ ከድንቅ የኢስላም ልጆች ጋር በመሆን ዲኔን አላስደፍርም፤ ኢስላሜን ለጠላት አሳልፌ አልሰጥም በማለት በሀሰት ተወንጅሎ ከ አምስት አመታት በላይ በእስር ያሳለፈ ሲሆን፣ በአሁኑ ሰዓት ከእስር ተፈቶ በጠ/ሚኒስተር ዶ/ር አብይ አህመድ በተዋቀረው የኢትዬጲያ ሙስሊሞች ተቋማዊ ለውጥ የጋራ ኮሚቴ ውስጥ የኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ በመሆን እያገለገለ ይገኛል።

አስሰላሙ አሌይኩም ወራህመቱላሂ ወበረካቱሁ
ወደ እኔ ድህረ ገጽ እንኳን በሰላም መጣችሁ እያልኩኝ፣ በገጾቼ ላይ የተለያዩ ለሙስሊሙ ማህበረሰብ ይጠቅማሉ ብዬ የማስባቸውን ቪድዮዎች፣ፅሁፎች እንዲሁም የተለያዩ ፖስቶችን በአላህ ፍቃድ የምለቅ መሆኑን እያስታወቅኩኝ፤ እርስዎንም ይህን ድህረ ገፅ ለወዳጅ ዘመድዎ እንዲሁም በብዙሀን መገናኛ ገጾቻችሁ ላይ ሼር በማድረግ የምንዳው ተካፋይ እንዲሆኑ እጋብዛለሁ።

የተለመደው መልካም ዱዓዎቻችሁም እንዳይለየን።

ኡስታዝ አቡበክር አህመድ